ቅደመ ታሪክ ላስ ቬጋስ | Las Vegas

ሰላም የdelalaw.biz ቤተሰቦች! ዛሬ ደግሞ ስለ አንዲት አስገራሚ ከተማ ታሪክ እንነግራችኋለን – ስለ ላስ ቬጋስ ማለት ነው! ይቺ ከተማማ… በቃ በምድረ በዳ ላይ እንደ አንድ የውሃ ጉድጓድ ብቅ ብላ፣ ዛሬ ደግሞ የግርምት እና የመዝናኛ ከተማ ሆና ዓለምን እያሳየች ያለች ድንቅ ናት። እስቲ ጉዞአችንን ወደ ኋላ እንጀምር!

ከ12,000 ዓመታት በፊት ሰዎች አሁን ላስ ቬጋስ በምትባልበት አካባቢ ይኖሩ እንደነበር ተረጋግጧል! እነዚህ ሰዎችማ ፓሌኦ-ህንድያን ( Paleo-Indians) ይባላሉ። ከእነሱ በኋላ ደግሞ የፓዩት ጎሳዎች (Paiute -Indians) መጡና በተራሮችና በሸለቆዎች መካከል እየተዘዋወሩ ኑሯቸውን ይመሩ ነበር።

ወደ 1829 አካባቢ ስንመጣ ደግሞ ራፋኤል ሪቬራ የሚባል አንድ ጀግና ስፔናዊ ይህንን አካባቢ ለመጀመሪያ ጊዜ በአውሮፓውያን ዘንድ አስተዋወቀ። ለምን መሰላችሁ? ከኒው ሜክሲኮ(New Mexico) ወደ ሎስ አንጀለስ (Los Angeles) በሚወስደው የንግድ መስመር ላይ ውሃ ጥም ስለተሰማቸው እዚህ አካባቢ አረፍ ብለው ነበር። እናም ቦታውን “ላስ ቬጋስ” ብለው ሰየሙት – የስፔንኛ ቃል ሲሆን ትርጉሙም “ሜዳዎች” ማለት ነው። በዚያን ጊዜ እዚህ አካባቢ ብዙ የውሃ ምንጮችና ለምለም መሬት ነበረ ይባላል።

ዓመተ ምህረቱን ወደ 1905 እናምጣውማ! በዚህ ጊዜ አንድ የባቡር መንገድ ከሎስ አንጀለስ (Los Angeles) እስከ ሶልት ሌክ ሲቲ (Salt lake) ድረስ ሊሰራ ታቅዶ ነበር። እናም ላስ ቬጋስ ለባቡሩ እንደ ማረፊያ ጣቢያነት ተመረጠች። ይህቺ ትንሽዬ ማቆሚያ ብዙ ሰዎችን ወደዚህ ምድረ በዳ መሳብ ጀመረች!

ከዚያ በኋላ በ1931 ዓ.ም. ደግሞ ታላቁ የቦልደር ግድብ (አሁን ሁቨር ግድብ በመባል ይታወቃል Hoover Dam) መስራት ተጀመረ። ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣት ወንዶችን ለስራ ወደ ላስ ቬጋስ ጎረፈ። ለእነዚህ ሰራተኞች መዝናኛ ቦታዎች ያስፈልጉ ስለነበር ትያትር ቤቶችና… ቁማር ቤቶች ጀመሩ! አብዛኛዎቹን የሰሩት ደግሞ “ማፍያ” ወይንም Mob የሚባሉት ቡድኖች ነበሩ ይባላል። (ወሬ ነው እንዳትይዙኝ! 😉) mob museum ሄዶ ማረጋገጥ ይቻላል፤ ደግሞ ለዱርዬም ሙዚየም ካላቹ አዎ ነው መልሱ።

በግድቡ ምክኛት ኤሌክትሪክ ሃይል በቅርበት መገኘት ደግሞ በላስ ቬጋስ ሌላ ምዕራፍ ከፈተ። ዝነኛው “ስትሪፕ” እየተባለ የሚጠራው አካባቢ በብዙ አዳዲስ ሆቴሎችና የቁማር ቤቶች መሞላት ጀመረ። ላስ ቬጋስ በድንገት ከአንዲት በረሃማ ማቆሚያ ወደ ዓለም አቀፍ የመዝናኛ ማዕከልነት ተቀየረች!

ስለ “ሲን ሲቲ” ስንናገር ግን… በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ቁማር እና ዝሙት በላስ ቬጋስ በስፋት ይካሄድ ስለነበር “ሲን ሲቲ” (የኃጢአት ከተማ) የሚል ቅጽል ስም ተሰጣት። ነገር ግን ይህንን ስም ስናነሳ በአሁኑ ጊዜ በላስ ቬጋስ ከተማ ውስጥ ዝሙት በህግ አይፈቀድም። ሆኖም በዙሪያዋ ባሉ አንዳንድ አካባቢዎች እንደሚፈቀድ ይታወቃል። ብዙ ሰዎች በስህተት በላስ ቬጋስ ህጋዊ ነው ብለው ያስባሉ።

እንግዲህ ይህቺ ናት የላስ ቬጋስ አጭር ታሪክ! ከጨለማ ምድረ በዳ ተነስታ በብርሃን የተንቆጠቆጥች፣ ለውሃ ጥም ማረፊያ ተጀምራ ለመዝናኛ የመታቋምጥ – ላስ ቬጋስ በእውነትም አስገራሚ ከተማ ናት!

ይህን ታሪክ እንደወደዳችሁት ተስፋ እናደርጋለን! ለተጨማሪ አስደሳች መረጃዎች delalaw.biz ን ይጎብኙ!

Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *